Oct 31, 2012

ኢሳያስ አፈወርቂ ሲቪል ኤርትራውያንን መሣርያ ማስታጠቅ ጀመሩ

 ዘመቻው ኤርትራውያንን ፍርኃትና ግራ መጋባት ውስጥ ከቷል

በዮሐንስ አንበርብር

የኢሳያስ አፈወርቂ መንግሥት ካለፈው የመስከረም ወር መባቻ ጀምሮ ዋና መዲናዋን አስመራን ጨምሮ በኤርትራ ዋና ዋና ከተሞች የሚገኙ ከ15 ዓመት በላይ የሆናቸው ኤርትራውያንን AK- 47 በመባል የሚታወቀውን ክላሽንኮቭ የጦር መሣርያ በግዳጅ ማስታጠቅ ጀመረ፡፡ በአስገዳጅነት የተጀመረው የማስታጠቅ ዘመቻ የአገሪቱን ዜጐች ፍርኃትና ግራ መጋባት ውስጥ እንደከተታቸው ዜናውን ይፋ ያደረገው የፈረንሳይ ሚዲያ ገልጿል፡፡ በኤርትራና በኤርትራውያን ላይ መጽሐፍ እስከ ማሳተም የደረሰው ጋዜጠኛ ሊዎናርድ ቪንሰንት በአገሪቱ በመዘዋወር በርካታ ነዋሪዎችንና የፖለቲካ ተንታኞችን ያነጋገረ ሲሆን፣ ኤርትራውያን አገራቸውን በንቃት እንዲጠብቁ በሚል የተጀመረ ዘመቻ ቢሆንም፣ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ ካለው ድህነት አንፃር ሲመዘን ግን ፕሬዚዳንት ኢሳያስ በራሳቸው ፍላጐት አንገታቸውን ለገመድ እየሰጡ ነው ለማለት የሚያስደፍር ዘመቻ ነው ብሎታል፡፡


ጋዜጠኛው በአስመራ እንዲሁም ሦስተኛዋ የኤርትራ ትልቅ ከተማ እንደሆነች በሚነገርላት ከረን በተዘዋወረበት ወቅት በርካታ ኤርትራውያን በሚኖሩባቸው አካባቢዎች በሚገኙ ቀበሌዎች ተሠልፈው የጦር መሣርያ ሲረከቡ መመልከቱን ገልጿል፡፡

አንዳንድ ነዋሪዎችም ስማቸው እንዳይጠቀስ በማስጠንቀቅ ያለውን ሁኔታ አስረድተውታል፡፡ ‹‹ስማችንንና አድራሻችንን ከመዘገቡ በኋላ በፕላስቲክ የተሠራ ካርድ ይሰጡናል፡፡ ይህም መሣርያውን ለመረከባችን ማስረጃና መታወቂያ እንደሆነ በመግለጽ፣ አገራችሁንና መሬታችሁን ከወረራ ነቅታችሁ ጠብቁ የሚል ትዕዛዝ ይሰጡናል፤›› ሲል ስሙ የተደበቀለት ወጣት ተናግሯል፡፡

‹‹አባቴ የ65 ዓመት አዛውንት ነው፡፡ የቀበሌው ባለሥልጣናትና ካድሬዎች እሱንና የዕድሜ እኩያ የሆኑ ጓደኞቹን በመጥራት የጦር መሣርያዎችን እንዳከፋፈሏቸውና አገራችሁን ከጠላት ጠብቁ እንዳሏቸው፣ ከፍርኃት የተነሳም ምንም ዓይነት ጥያቄ እንዳላቀረቡ ነግሮኛል፤›› ሲል በካናዳ በስደት ኑሮ ላይ የሚገኝ ስሙ ለቤተሰቦቹ ደኅንነት ሲባል ያልተጠቀሰ ወጣት ለጋዜጠኛው ገልጾለታል፡፡

ፊልሞን የተባለ ሌላ ወጣት በበኩሉ አባቱ የምሕንድስና ባለሙያ እንደሆኑና የቀበሌ ባለሥልጣናቱ መሣርያ እንዲረከቡ ሲጠሩዋቸው እንቢ እንዳሉዋቸው፣ በዚህም ምክንያት በመንግሥት ድጐማ የሚቀርበውን የምግብ እህል ለመግዛት የተሰጣቸውን የሬሽን ካርድ እንደሚነጥቁዋቸው ዝተው መሄዳቸውን ገልጿል፡፡ መሣርያውን ለተረከቡ ነገር ግን እንዴት መጠቀም እንዳለባቸው ለማያውቁት ከሣዋ ወታደራዊ ካምፕ በሚላኩ ወታደሮች በየሳምንቱ ቅዳሜና እሑድ ሥልጠና እንደሚሰጣቸውም ዘገባው ያመለክታል፡፡

በቀበሌ ደረጃ ከሚደረገው የማስታጠቅ ዘመቻ በተጨማሪ በተለያዩ የመንግሥት መሥርያ ቤቶችም እንደቀጠለ የሚያትተው የዜና ምንጩ፣ ባለፈው ጥቅምት 8 ቀን 2005 ዓ.ም. የአገሪቱ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ሠራተኞች በአስመራ ኤክስፖ ሴንተር ተገኝተው መሣርያውን እንደተረከቡ ገልጿል፡፡ ቀጥሎ በነበሩት ሁለት ቀናት ደግሞ የትምህርትና የግብርና ሚኒስቴር ሠራተኞች መሣርያውን እንዲታጠቁ መደረጉን ያትታል፡፡

በተለይ ባለፈው መጋቢት 2004 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ጦር በኤርትራ አፋር ክልልና በባድመ አካባቢዎች ከወሰደው ወታደራዊ ጥቃት በኋላ በኤርትራ ውጥረትና ሥጋት መንገሱን ዘገባው ይገልጻል፡፡ ሴንተር ኦፍ አፍሪካን ስተዲስ የተባለ ድርጅት ባልደረባ የሆነው ዴቪድ ቦዚኒ የተባለ ሲዊዘርላንዳዊ ለዜና አውታሩ በሰጠው አስተያየት፣ ኤርትራ ውስጥ መሣርያ ማስታጠቅ አዲስ አይደለም፣ ነገር ግን አሁን  አዲስ የሆነው የከተማ ነዋሪዎችን ማስታጠቅ መጀመሩ ነው ብሏል፡፡

‹‹በግብፅና በሊቢያ የተደረገው አመፅና ውጤቱ የፕሬዚዳንት ኢሳያስን የቅርብ ወዳጅ መሪዎች አሳጥቷል፡፡ ይህንን ተከትሎም የኤርትራ ወጣቶች ከኤርትራ ውጭ በመሆን ተመሳሳይ አመፅን በአገራቸው ላይ ለመፍጠር እየተደራጁ መሆኑ በፕሬዚዳንት ኢሳያስ ላይ መደናገጥን ፈጥሯል፤›› የሚለው የጥናት ባለሙያ፣ ‹‹አሁን የሚካሄደው የማስታጠቅ ዘመቻ አመፅ ከመነሳቱ በፊት ኤርትራውያንን ሥጋት ወስጥ በመክተት አርቴፊሻል ውጥረትን በአገሪቱ በመፍጠር ሥልጣናቸውን የማቆያ ስልት ነው፤›› ብሏል፡፡

ሌሎች ባለሙያዎች በበኩላቸው የማስታጠቅ ዘመቻውን ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ራሳቸውን ጠልፈው የሚጥሉበት ሊሆን ይችላል በማለት የተናገሩ ሲሆን፣ በተለይም በአገሪቱ ያለው የከፋ ድህነት በኤርትራውያን ውስጥ ለፈጠረው የተዳፈነ ትዕግስት ማጣትና የኤርትራ ወጣቶች ጥምረት ለለውጥ በሚል ስያሜ ለተጀመረው እንቅስቃሴ ምቹ ሁኔታን ሊፈጥር ይችላል ብለዋል፡፡

31, october 2012
ethiopian reporter.
Previous Post
Next Post

0 comments: