Nov 3, 2012

በሰዋስወ ብርሃን ቅ/ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ ትምህርት ከተቋረጠ ከሁለት ወራት በላይ ኾኖታል.

  • ደቀ መዛሙርቱ በዋና ዲኑ ቀሲስ በላይ መኰንን የተዘጋጀውን “የኮሌጅ ደንብና ሥነ ሥርዐት ለማክበር ቃል የሚገባበት ቅጽ” ካልፈረሙ ምዝገባ እንደማይጀመር ተነግሯቸዋል፤ /የቅጹን ተ.ቁ (8) ይመልከቱ/፡፡
  • የስድሳ ዓመት ዕድሜ ባስቆጠረ ሥርዐተ ትምህርት ወደ ኮሌጅ ደረጃ አድጓል የተባለው ተቋሙ “የዲግሪ ፕሮግራም ለመጀመር ዝግጅት አጠናቀናል” ብሏል፤ ደቀ መዛሙርቱ በበኩላቸው “ሥርዐተ ትምህርቱ አልተለወጠም፤ ኮሌጁም አላደገም፤ ቦታው አልሚ አላገኘም” እያሉ ነው፤
  • ደቀ መዛሙርቱ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱን ውሳኔ በጉጉት እየተጠባበቁ ነው
  • የኮሌጁ ዋና ዲን ቀሲስ በላይ መኰንን ለፕሮቴስታንቱ የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር ሺፈራው ተክለ ማርያም÷ “ዘመነ ማቴዎስ የተጠሩበት[ን] ሐዋርያዊ አገልግሎት የበለጠ የሚፈጽሙበትና የሚያስፈጽሙበት ዘመን እንዲኾንልዎ ምኞቴን ስገልጽ በታላቅ አክብሮት ነው፤” በማለት በኮሌጁ የፕሮቶኮል ደብዳቤ የመልካም ምኞት መግለጫ ጽፈውላቸዋል፤ /ሰነዱን ይመልከቱ/፡፡

(ደጀ ሰላም ጥቅምት 24/2005 ዓ.ም፤ ኖቬምበር 3/2012/ READ THIS NEWS IN PDF)፦ የዘንድሮው የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ 31 መደበኛ ስብሰባና የጥቅምት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ውሳኔዎችና የአቋም መግለጫዎች አጽንዖት በሰጠባቸው የሰላም፣ መልካም አስተዳደር፣ የመንፈሳዊ እና ማኅበራዊ ልማት አጀንዳዎች ውስጥ ለተያዙት ዕቅዶች መሳካት የትምህርትና ሥልጠና ተቋሞቻችን፣ የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መዋቅሮቻችን ከፍተኛ አደራ ተጥሎባቸዋል፡፡

የተጣለባቸውን አደራ እንዲወጡም አስፈላጊው በጀት ተመድቦላቸው በባለሞያ እንዲደራጁ፤ ዘመኑን የዋጀ ግልጽነት፣ አሳታፊነትና ተጠያቂነት ያለበት ቀልጣፋ አሠራር እንዲዘረጉ፣ ከተልእኳቸው ጋራ የተገናዘበ የረጅምና አጭር ጊዜ ስትራቴጂያዊ ዕቅዶችን እንዲቀርጹ፣ በየደረጃው የሚያገለግል ወጥ ሥርዐተ ትምህርት እንዲያዘጋጁ፣ ከሠልጣኝ ደቀ መዛሙርት አመላመል ጀምሮ እስኪመረቁና በምደባም ወቅት በዕቅድ ላይ ተመሥርቶ በሚካሄደው የክትትል፣ ድጋፍና ግብረ መልስ ሥርዐት እንዲጠናከሩ ተወስኗል፡፡

በ31ው አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ላይ “ለውጥ እንዲመጣ ከተፈለገ ሥልጠና መጀመር ያለበት ከቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ነው” የሚልና በሁሉም ጉባኤተኛ የተደገፈ የዝግጁነት መንፈስ እንደ ብፁዕ አቡነ ዳንኤል ካሉት አባቶች መደመጡ የሚያበረታታ ነው፡፡
አብነት ት/ቤቶች፣ ሰንበት ት/ቤቶች፣ የካህናት ማሠልጠኛዎች እና ኮሌጆች ዐይነተኛ የትምህርትና ሥልጠና ተቋሞቻችን፣ የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መዋቅሮቻችን ናቸው፡፡ የትምህርትና ሥልጠና መምሪያ፣ የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ፣ የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ እኒህን ተቋሞቻችንና መዋቅሮቻችንን በበላይነት የማስተባበርና መምራት ሓላፊነት የተጣለባቸው የመንበረ ፓትርያርኩ ከፍተኛ አስፈጻሚ አካል ቢሆኑም አንድም የጠየቁትን በጀት፣ የተሟላ የሰው ኀይልና አደረጃጀት በማጣት አልያም በሓላፊነት በተመደቡት ግለሰቦች የሃይማኖት፣ አስተሳሰብ ይኹን ተግባር መጻጉዕነት የተነሣ ተልእኳቸውን በአግባቡ እንዳልተወጡ በሰሞኑ ታላላቅ ግምገማዎቻችን ተደጋግሞ የተወሳ ጉዳይ ነው፤ በቀጣይም ከተጣሉት የተቋማዊ ለውጥ ስትራቴጂያዊ ግቦች አኳያ ሂደቱን መደገፍ በሚገባቸውና በሚችሉበት ቁመና ላይ ይገኛሉ ለማለት በእጅጉ አዳጋች ነው፡፡
በአገር ዓቀፍ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰንበት ት/ቤቶች ጉባኤ ምሥረታ ሂደት ላይ የሚገኘው የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ÷ የአምስት ዓመት ስትራቴጂያዊ ዕቅድ በመቅረጽ፣ የወጣቶች ፖሊሲ እና የሰንበት ት/ቤቶች ወጥ ሥርዐተ ትምህርት ለማዘጋጀት የወጠነ ቢሆንም ለሥራው ማስፈጸሚያ ያቀደውንና የሚበቃውን ያህል በጀት ማግኘት እንዳልቻለ እየገለጸ ነው፡፡
በየጊዜው የቤተ ክርስቲያናችን የዕውቀት ምንጭና የሠለጠነ ሰው ኀይል መሠረት የኾኑትን አብነት ት/ቤቶቻችን፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋሞቻችንን (ሦስቱን ኮሌጆቻችንን)ና የካህናት ማሠልጠኛዎቻችንን በበላይነት የመምራትና አስፈላጊውን ድጋፍ የመስጠት ሓላፊነት ያለበት የትምህርትና ማሠልጠኛ መምሪያ በየዓመቱ ከኮሌጆቹ ብቻ የሚመረቁትን ደቀ መዛሙርት በአህጉረ ስብከት ከመመደብ የዘለለ የሥራ ክንውን ሊኖረው እንዳልቻለ በበጀት ዓመቱ የቀረበው ሪፖርት ያሳያል፡፡ ሌላው ቀርቶ የዘመናዊ ትምህርት መስፋፋት እየተጋፋው ህልውናው አደጋ ውስጥ ለገባው የአብነት ትምህርት ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያለው መለኪያ ተበጅቶለት ወጥ ሥርዐተ ትምህርት እንዲዘጋጅለት፣ ለአብነት መምህራኑ ከኑሮው ውድነት ጋራ የተመጣጠነ ቋሚ ደመወዝ÷ ለደቀ መዛሙርቱም ቀለብ፣ አልባሳት፣ ምቹ መማሪያና ማደሪያ፣ የስብከት ዘዴን ጨምሮ ተጓዳኝ የክህሎት ሥልጠናዎች እንዲሰጣቸው፣ በመደበኛ ጊዜ ከጉባኤ ቤት እየተመረቁ በየአህጉረ ስብከቱ እንዲመደቡ ውሳኔዎች በተላለፉበት ወቅት መምሪያው ምን ያህል የአብነት ት/ቤቶች፣ መምህራንና ተማሪዎች እንዳሉን እንኳ በቅጡ የሚያሳይ የተሟላ መረጃ የለውም፡፡
ላለፈው ጊዜ የመምሪያው ሓላፊዎች በየጊዜው መቀያየር እና የትኩረት መነፈግ እንደ ምክንያት ቢጠቀስ እንኳ የአዎንታዊ ለውጥ ነፋስ እየነፈሰ ባለበት በአሁኑ ወቅት ግን ያለ ብቃታቸው በመምሪያው ሓላፊነት የተሾሙትና ከአቡነ ጳውሎስ ሥርዐተ ቀብር በኋላ በአሜሪካ ያደፈጡት አባ ሠረቀ ብርሃን ወልደ ሳሙኤል በሥራ ገበታቸው ላይ አለመገኘት ከዚህ በኋላ በትዕግሥት ሊታይ የሚገባው አይደለም፡፡ ያለፈው ዓመት የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ጥንተ አብሶን በተመለከተ በእመቤታችን ቅድስና ላይ ያላቸውንና እርሳቸውም በሊቃውንት ጉባኤ ፊት በቃል የመሰከሩትን እምነታቸውን በጽሑፍ እንዲያቀርቡ የተላለፈባቸውን ውሳኔ በተግባር ሳይፈጽሙ በእጅ ጥምዘዛ ያጻፉትን “የነጻነት ማረጋገጫ ደብዳቤ” ዳግመኛ እንዲጤን ያስፈልጋል፡፡
በስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ በኩል የመምሪያው ሓላፊ መጋቤ ብሉይ አእመረ አሸብር በድሬዳዋ፣ በሐዋሳ፣ በነገሌ ቦረና አህጉረ ስብከት ጎልቶ ይታይ የነበረውን የሕገ ወጥ ሰባክያን እንቅስቃሴ ጸጥ ረጭ ስለማድረጋቸው በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ሳይቀር የተመሰከረላቸውን የመምሪያውን ሠላሳ ሰባክያነ ወንጌልና የፀረ ተሐድሶ ጥምረት አባላት በ31ው አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ላይ በማሳጣቱ፤ በምትኩ መምሪያውን የሚወክል በዕቅድ ክንውን የሚገለጽ ሪፖርት ሳይሆን ራሱ እንደ “ጉባኤ አርድእት” ያሉት ሕገ ወጥ ቡድኖች ዋና መሪና አስተባባሪ ኾኖ ሳለ ሌሎችን በቡድንተኝነት የዘለፈበትን ዲስኩር በማሰማቱ፤ በቅርቡ ፍ/ቤት በሰጠው የመጨረሻ ውሳኔ መሠረት ከቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ በሕገ ወጥ መንገድ ተመዝግቦ ያገኘው ዲግሪ እንደሚያዝበት ለተነገረው እንደ አሰግድ ሣህሉ ላሉ የለየላቸው መናፍቃን ከአንድም ሁለት ጊዜ የፈቃድ እና የማበረታቻ ደብዳቤ በመጻፉ በተቀሰቀሰበት ብርቱ ተቃውሞ ሠርቶ ለማሠራት ባለመቻሉ ከሓላፊነቱ እንዲነሣ ተወስኖበታል፡፡
አባ ሠረቀ ብርሃን ወልደ ሳሙኤል በዋና ሓላፊነት በሚመሩት የትምህርትና ማሠልጠኛ መምሪያ ሥር ከሚገኙት የከፍተኛ ትምህርት ተቋሞቻችን አንዱ የሰዋሰወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ አንዱ ነው፡፡ ፖለቲካዊ አቋሞቻቸውን እና ሃይማኖታዊ እምነቶቻቸውን ሲያምታቱት እንደ ቆዩት አባ ሠረቀ ብርሃን ሁሉ በጥንቃቄ ሊታዩ የሚገባቸው ሌላው ግለሰብ የኮሌጁ ዋና ዲን ቀሲስ በላይ መኰንን ናቸው፡፡
በአሁኑ ወቅት የሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ ዋና ዲን የኾኑት ቀሲስ በላይ በሓላፊነት ከተመደቡበት ካለፉት ስድስት ወራት ወዲህ÷ የኮሌጁን ተሽከርካሪ፣ የነዳጅና ተጓዳኝ ወጪዎች ለግል ፍላጎታቸው ብቻ በመጠቀም (በአንድ ወር ብቻ እስከ ብር 13,000 ‹ለነዳጅ› ወጪ ስለማድረጋቸው ተሰምቷል)፤ በኮሌጁ ቅጥር ግቢ የሚገኘውንና በ1935 ዓ.ም በግርማዊት እቴጌ መነን ለእጓለ ሙታንና የአርበኞች ልጆች በተቋቋመው ዐጸደ ሕፃናት ስለሚማሩትና ስለሚያድጉት ሕፃናት ቁጥር የተሳሳተ መረጃ እየሰጡ የግል ጥቅማቸውን በማካበት (በወር እስከ ብር 17,000 ይገመታል)፤ ካለፈው ዓመት ሰኔ ወር አጋማሽ ጀምሮ “ለኮሌጁ እድሳት ለማድረግ፣ ለዲግሪ ፕሮግራም ለሚደረገው ዝግጅት መምህራን ለማዘጋጀት” በሚል ኮሌጁ ተዘግቶ እስከ አሁን በቆየባቸው አራት ወራት ለ66 ደቀ መዛሙርት ለእያንዳንዳቸው ሊደርሳቸው የሚገባውን ብር 300 ‹በመቀናነሳቸው› በአጠቃላይ መላው የኮሌጁ ማኅበረሰብ አባላት ከጥቅምት ወር ጀምሮ ከኮሌጁ አስተዳደር ጀምሮ እስከ መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት በደረሰው አቤቱታቸው እንደገለጹት “ለአንጋፋው ቦታ በማይመጥነው አስተዳደራቸው” ጥያቄ እየቀረበባቸው ይገኛል፡፡
ከ1946 ዓ.ም ጀምሮ የቤተ ክርስቲያን የከፍተኛ ትምህርት ሥልጠና እንዲሰጥበትና በወቅቱ አጠራር “የኢትዮጵያ መንግሥት መንፈሳዊ ጉባኤ ጠቅላይ ጽ/ቤት” እንዲቆጣጠረው የተደረገው ተቋሙ 60 ዓመታትን ያስቆጠረ ቢሆንም ሥርዐተ ትምህርቱም ይኹን ደቀ መዛሙርቱ በማደሪያነት የሚገለገሉባቸው መኝታ ክፍሎች መሻሻል እንዳልተደረገባቸው ደቀ መዛሙርቱ ይናገራሉ፡፡ የትርጓሜ እና የሴሚናር/ኮርስ/ በሚል በተከፈሉ የትምህርት መርሐ ግብሮች በአመዛኙ ከአብነት ት/ቤት የወጡ መምህራንና በአገልግሎት ላይ የሚገኙ ካህናትን እየተቀበለ ለሦስት ዓመት ሲያሠለጥን የቆየው ማሠልጠኛ ተቋሙ ከ2001 ዓ.ም ጀምሮ በሥርዐተ ትምህርት ዝግጅቱ፣ በአስተዳደሩ ይኹን በተቋማዊ ገጽታው አንዳችም ለውጥ ሳያካሂድ ነበር ወደ ኮሌጅ ደረጃ እንዲሸጋገር የተደረገው፡፡
የኮሌጁ ዋና ዲን ቀሲስ በላይ ኮሌጁ በ2004 ዓ.ም በቀንና በማታው ክፍለ ጊዜ በድምሩ 152 ተማሪዎችን ባስመረቀበት ወቅት ባደረጉት ንግግር ተቋሙ የሚያሠለጥናቸው ደቀ መዛሙርት ወደ ኮሌጁ ከመምጣታቸው በፊት በገዳማትና አድባራት ሲያገለግሉ የቆዩ የጉባኤ መምህራን በመኾናቸው የኮሌጁን ሥልጠና “የአቅም ግንባታ ፕሮግራም ብለን መውሰድ እንችላለን” ማለታቸውን የሚያስታውሱት ደቀ መዛሙርቱ በአንጻሩ÷ ሥርዐተ ትምህርቱ፣ የትምህርት መርጃ ማቴሪያሎቹም ይኹኑ መምህራኑ÷ ደቀ መዛሙርቱ ካላቸው የዕውቀት ደረጃ ያነሱ፣ “ያንኑ ሥርዐተ ትምህርት እንኳ በአግባቡ ለማስኬድ የሚችሉ መምህራን እንኳ በበቂ የሌሉበት ነው” በማለት ምሬታቸውን ያስረዳሉ፡፡ አምና በአቅም ማነስ ማስተማራቸውን እንዲያቋርጡ ተደርገው የወጡ መምህራን በክረምቱ “አቅም ግንባታ ሳይደረግላቸው” ዘንድሮም ተመልሰው መምጣቸውን የሚናገሩት ደቀ መዛሙርቱ “በተለይ በዶግማ ዙሪያ የሚመጥነን ትምህርት እየተሰጠን አይደለም፤ ብዙ ሊቃውንት አሉና ስለምን እነርሱ እንዲመጡ አታደርጉም ብንል ‹በዶግማ ሦስት ዐይነት አስተምህሮ ነው ያለው› የሚል መምህር ነው ያመጡልን” በማለት በዋና ዲኑ ላይ ያላቸውን ጥርጣሬ ይገልጻሉ፡፡
በ31ው የመ/ፓ/አጠ/ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ መደበኛ ስብሰባ ላይ የቀረበው የኮሌጁ ሪፖርት ለቢሮ፣ ለመማሪያና ለተማሪዎች ማደሪያ ባለሁለት ፎቅ ሕንጻ ተሠርቶ መመረቁን፣ ከገበያ ውድነት የተነሣ ለተማሪዎች ቀለብና ልዩ ልዩ ወጭ የተያዘው በጀት በቂ ባለመኾኑ በአዲስ መልክ የተዘጋጀውና በቦርዱ ተቀባይነት ያገኘው በጀት ለቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ መቅረቡን ያትታል፡፡ ይኹንና ደቀ መዛሙርቱ እንደሚያስረዱት ከተሠራ ስድሳ ዓመት ያስቆጠረው የመኝታ ክፍላቸው ጣሪያ በላያቸው እያፈሰሰ፣ የሕክምና አገልግሎት በሌለበት ኹኔታ በርጥበት የሚወረዛው ግድግዳም በተለይም አዲስ ገቢ ደቀ መዛሙርትን ለከፍተኛ የጤና ጠንቅ እየዳረጋቸው ነው፡፡
ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ አንድ የብሉያት ትርጓሜ የመጨረሻ ዓመት ተማሪ ስለዚህ ኹኔታ ሲያስረዱ÷ “ከምንም በላይ የእኛ ዓላማችን ትምህርት ስለሆነ ችግራችን አእምሯዊ ቀለብ ማጣት ነው፡፡ በሌላ በኩል አካላዊ ጤንነታችንን የሚጠብቅልን ነገር የለም፤ አመጋገባችን ያን ያህል ነው፤ በተለይ ደግሞ በሕክምና ዙሪያ ያለው ችግር፡፡ የአንደኛ ዓመት ተማሪዎች እንደገቡ በሽታ ላይ ነው የወደቁት፤ ሞግዚቱን ጠርተን መኪና ስንጠይቅ አንዱን ፒክ አፕ ዋና ዲኑ ይዘውታል፤ ሁለተኛውን ሌሎች ሠራተኞች ወስደውታል ተብለን በትራንስፖርት ታክሲ ይዘናቸው ጦር ኀይሎች በግል የሚሠሩ ሐኪም ናቸው ተብለን ሄድን፤ እዚያ ስንደርስ ለተቋሙ ሕክምና ውል የለንም አሉን፤ ወደ ዐማኑኤል ይዘናቸው ሄድን፤” ይላሉ፡፡ ሌላውም ደቀ መዝሙር÷ “እንደ ተቋምነቱ ተቋማዊ ክብካቤ የለውም፤ ምን ይማራሉ÷ ማን ያስተምራቸዋል÷ ምን ያነባሉ ብሎ የሚጠይቅ የለም፤ እኛን የመቅረጽ ሥራ እየተሠራ አይደለም፤ አርባ አምስት ሚሊዮን ሕዝብ የሚጠብቀን ተክሎች፣ አገልጋዮች ነንኮ! ምን ያህል ዘመኑን የዋጁ ናቸው፤ ምን እናድርግላቸው የሚል ምንም ዐይነት ደ[ዳ]ሰሳ ግን የለም፤ እንዲሁ ገባን፤ ምን ይበላሉ፤ ምን ይማራሉ፤ እንዴት ይኖራሉ የሚል ሳይኖር ሰዓቱ ሲደርስ ብቻ ተመረቍ፤ ውጡ ነው የሚሉን፤” ብለዋል፡፡
በተያዘው የትምህርት ዘመን የማታው መርሐ ግብር ተማሪዎች መስከረም 10 ቀን ተመዝግበው የመማር ማስተማሩ ሂደት ጀምሯል፡፡ መደበኞቹ የትርጓሜ ደቀ መዛሙርት እና የሴሚናር ኮርሰኞች ግን ከመስከረም 28 ቀን ጀምሮ በተቋሙ የተገኙ ቢኾንም ወደ ትምህርታቸው መግባት አልቻሉም፤ ምንም ዐይነት ምዝገባም አልተካሄደላቸውም፡፡ “እድሳት እናደርጋለን፤ ለዲግሪው መርሐ ግብር የሚያስፈልጉንን መምህራን እናዘጋጃለን” በሚል ከመደበኛው ጊዜ ሁለት ወራት ቀደም ብሎ ሰኔ 15 ቀን 2004 ዓ.ም የተቋረጠው ትምህርት አራተኛ ወሩን አስቆጥሯል፡፡ “ያን ጊዜ የተገባው ቃል ሁሉ አልተፈጸመም፤ ሥርዐተ ትምህርቱ አልተዘጋጀም፤ ምንም የእድሳት እንቅስቃሴ አልተደረገም፤ ሁለቱን ወሩን ብንታገሥ እንኳ እንዴት ኮሌጁ ለአራት ወራት ይዘጋል ብለን ብንጠይቅ እዚህ ያሉት ሰዎችም ሊሰሙን አልቻሉም፤ በምትኩ እኛ እንዳንጠይቃቸው ዋና ዲኑ ከምክትል ዲኑ፣ ከአካዳሚክ ዲኑ፣ ከአስተዳደሩ፣ ከቁጥጥሩና ከተማሪዎች ተወካይ ጋራ ሳይመክሩና ሳያውቁት ብቻቸውን ያዘጋጁትን የኮሌጁን ደንብና ሥነ ሥርዐት ማስከበሪያ ቅጽ ካልፈረማችኹ አትመዘገቡም፤” እንዳሏቸው የገለጹት ደቀ መዛሙርቱ “እንድንናገር የሚያስገድደን ችግር ሳይፈታ፣ የደቀ መዛሙርት መማክርት ተቋቁሞ ያልመከርንበትን አትሰብሰቡ፤ አትነጋገሩ፤ አትፈራረሙ የሚለንን ቅጽ እንዴት እንፈርማለን?” በማለት በተለይ በቅጹ ተ.ቁ (8) ላይ የሰፈረውን አንቀጽ አጥብቀው ይኮንናሉ፡፡
ጥቅምት አምስት ቀን ደቀ መዛሙርቱን ስብሰባ የጠሩት ዋና ዲኑ “የፈለገ ፈርሞ ይማር ያልፈለገውን አባረው” ካሉ ወዲህ ችግራቸው በኮሌጁ አስተዳደር ይኹን በቦርዱ እንደማይፈታ በመረዳት ለመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ማመልከታቸውን የደቀ መዛሙርቱ ተወካዮች ተናግረዋል፡፡ አቤቱታቸውን ተከትሎ በጽ/ቤቱ ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ ተስፋዬ ውብሸት የተመራ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ሥራ አስፈጻሚ አካል ሁለት ጊዜ ወደ ኮሌጁ በመምጣት ከደቀ መዛሙርት እና ከአስተዳደር ሠራተኞች ጋራ ተወያይቷል፡፡ በዚህ ማጣራት ዋና ዲኑ ከምክትላቸው ጀምሮ ከሥራ ባልደረቦቻቸው ጋራ ተግባብተው እና ተቀናጅተው እንደማይሠሩ፤ ከሥርዐተ ትምህርት ዝግጅት ባሻገር በምግብ፣ በሕክምና በፋይል አያያዝ ሁሉ ችግሮች ስለመኖራቸው መረጋገጡ ታውቋል፡፡
ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ችግሩን ከተመለከተ በኋላ ጉዳዩ ውሳኔ እንደተላለፈበት ለደቀ መዛሙርቱ የተነገራቸው ቢሆንም ውሳኔው ምን እንደ ኾነ አልተነገራቸውም፤ ትምህርቱም አልተጀመረም፡፡ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱን ውሳኔ በጉጉት የሚጠባበቁት ደቀ መዛሙርቱ ውሳኔው ከሦስት ጥያቄዎቻቸው እና በአንጻራዊነት ካስቀመጧቸው ሦስት የመፍትሔ ሐሳቦች ጋራ እንደሚመጣጠን ተስፋ ያደርጋሉ፡፡ እኒህም፡-
  • ተቋሙ ኮሌጅ ከተባለ በኋላ የነበረው ሥርዐተ ትምህርት አልተለወጠም - የደቀ መዛሙርቱን ደረጃና ወቅቱን ያገናዘበ ሥርዐተ ትምህርት ቢቀረጽ፤
  • የቀድሞውን ሥርዐተ ትምህርት እንኳ በበቂ የሚያስኬዱ መምህራን የሉም - የመምህራኑ ግንዛቤ፣ ዕውቀት በሚሻሻለው ሥርዐተ ትምህርት ደረጃ እኛን ለመቅረጽ የሚያስችል እንዲኾን፤
  • የኮሌጁ የማስተማር ሂደትና የተቋማዊ አደረጃጀት ኹኔታ ማደግ በሚገባው ደረጃ እያደገ አይደለም - ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር በደቀ መዛሙርት ምረቃ በዓል ላይ የዲግሪ መርሐ ግብር እንደሚጀምር በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ፊት ቃል በተገባው መሠረት ቀድሞም መምህራን ነበርንና ሥልጠናችን በዲግሪ ደረጃ ቢያዝልን፤

የሚሉ ናቸው፡፡
ደቀ መዛሙርቱ ቀድሞም ለነበሩትና ካለፈው ዓመት መጨረሻ ጀምሮ ለተባባሱት ችግሮች የዋና ዲኑን ያህል ባይሆንም ከጥቅምት 2004 ዓ.ም አንሥቶ የኮሌጁ የበላይ ሓላፊ ሊቀ ጳጳስ የኾኑትን ብፁዕ አቡነ ያሬድን ጭምር መውቀሳቸው አልቀረም፡፡ ብፁዕነታቸው ከኮሌጁ ሊቀ ጳጳስነት በተጨማሪ በመ/ፓ/ጠ/ቤ/ክ የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያ እና የሶማሌ ሀ/ስብከትም ሊቀ ጳጳስ ናቸው - “ሊቀ ጳጳሱ ሰፊ አገልግሎት ይሰጡናል፣ በግል ሕይወታችን ሳይቀር እየተከታተሉ ይደግፉናል ብለን ተስፋ ጥለንባቸው ነበር፡፡”
ደቀ መዛሙርቱ ክፉኛ የሚወቅሷቸውና ከብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ ዕረፍት ወዲህ የራሳቸውን ፓትርያርክ ለማስቀመጥ ከሚሠሩት ቡድኖች አንዱን እንደሚወክሉ በስፋት የሚወራባቸው ቀሲስ በላይ መኰንን÷ እንደ ዋና ዲንነታቸው በኮሌጁ ያላቸውን ሓላፊነት ያልተወጡባቸው በዋናነት ከአቅም ጋራ የተያያዙና ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ መፍትሔ እንደሚሰጥባቸው የሚጠበቁ ምክንያቶች ቢኖሩም÷ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በብርቱ የሚነቀሱባቸው ሁለት ምክንያቶች ግን የሃይማኖታቸውን ርቱዕነት ጭምር የሚመለከቱ ናቸው፡፡
አንደኛው÷ ቀሲስ በላይ መኰንን በየዓመቱ መስከረም ወር በዋቄፈና እምነት በሚከበረው የኢሬቻ በዓል ላይ የአደባባይ ንግግር ከማድረግ ጀምሮ ያላቸው ቀጥተኛ ተሳትፎ፣ ተሳትፎው በተመልካቾቻቸው ላይ ስለ እርሳቸው ማንነት የፈጠረው መደናገር (የጎራ መደበላለቅ) ግን በአንድ ከፍተኛ የቤተ ክርስቲያናችን ትምህርት ተቋምና ቀደም ሲልም በከፍተኛ የአስተዳደር ሥልጣን ላይ ከነበረ ሓላፊ የማይጠበቅ በመኾኑ ግልጽ ማብራሪያ÷ ሐቁን ለመናገር ደግሞ ተዐቅቦ÷ የሚያስፈልገው እንደኾነ ብዙዎች እየተቹበት ያለ ጉዳይ ነው፡፡
ሁለተኛው÷ በአዲሱ ዓመት ዋዜማ በፕሮቴስታንት እምነት ተከታይነታቸው ለሚታወቁ አንድ ከፍተኛ የፌዴራል መንግሥቱ ባለሥልጣን (የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር ሺፈራው ተክለ ማርያም) የጻፉት የእንኳን አደረስዎ ደብዳቤ ከአዲስ ዓመት መልካም ምኞት የዘለለ ምክንያት እንዳለው የሚያስጠረጥር ኾኗል፡፡ በዋና ዲንነት በሚመሩት ኮሌጅ የፕሮቶኮል ደብዳቤ፣ በኮሌጁ የበላይ ሐላፊ ሊቀ ጳጳስና በኮሌጁ ማኅበረሰብ ስም የተጻፈው የቀሲስ በላይ መኰንን የአዲስ ዓመት መልካም ምኞት መግለጫ ጥርጣሬውን ያጫረው ዘመነ ማቴዎስ የሥራ፣ የብልጽግና፣ የምቾት እንዲኾን ለተጠቀሰው ሚኒስቴር ሚኒስትር ምናልባትም ለሌሎችም ባለሥልጣናት ስለጻፉ አይደለም፡፡ የመረጃ ምንጮቹን ጥርጣሬ ያጫረው “. . .የተጠሩበት ሐዋርያዊ አገልግሎት የበለጠ የሚፈጽሙበትና የሚያስፈጽሙበት ዘመን እንዲኾንልዎ ምኞቴን ስገልጽ በታላቅ አክብሮት ነው” በማለታቸው ነው፡፡
ቸር ወሬ ያሰማን፤
አሜን፡፡
3, November 2012
Deje Selam
Previous Post
Next Post

0 comments: