Dec 25, 2012

ስብሓት ነጋ ቤተ ክርስቲያን ልትበታተን እንደምትችል አስጠንቀቁ!!


  • ‹‹አሁን መጠንቀቅ ያለብን ትበታተናለች፡፡ ብዙ የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያናት በኢትዮጵያ ሊፈጠሩ ይችላሉና በቅንነት ገምግመን እንዴት እንሂድ? እንቀይስ? ጊዜው አሁን ነው፡፡››
  • ‹‹በሂወት ያላችኹ ጳጳሳት ምሕረትን አውርዱላት፡፡››
/አቶ ስብሓት ነጋ ስለ አቡነ ጳውሎስ ሞት በተዘጋጀው የሐዘን መግለጫ መዝገብ ላይ ካሰፈሩት/
 ይህን መረጃ ያገኘነውና የምናቀርብላችኹ÷ ከብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪክ አቡነ ጳውሎስ ኅልፈት በኋላ የቤተ ክርስቲያንን አንድነት በዕርቀ ሰላም በማረጋገጥ እና ስድስተኛውን ፓትርያሪክ በመሾም መካከል የተከፋፈሉ የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት አቋም መልክ ለይቶ በወጣበት ኹኔታ ውስጥ ነው፡፡ ከዚህም በመነሣት ተቋማዊ አነዋወራችን የሚያስጨንቃቸው ኦርቶዶክሳውያን ቤተ ክርስቲያን በመስቀለኛ መንገድ ላይ እንደኾነች በማመን ከፓትርያሪክ ምርጫው በፊት ሰላሟና አንድነቷ እንዲቀድም የተባበረ ድምፃቸውን እያሰሙ ነው፡፡
አቶ ስብሓት ነጋ
አቶ ስብሓት ነጋ
ቤተ ክርስቲያን አገራዊ ግዴታዋን ስትወጣ እንደነበረችና ለወደፊትም ታላቅ ሚና ሊኖራት እንደሚችል የጻፉት የኢትዮጵያ የሰላምና ልማት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተርና የህወሓት መሥራቹ አቶ ስብሓት ነጋ÷ ‹‹አሁን የት ነች ብለን እናስብ፤ ደኅና ናት ወይ?›› በማለት ይጠይቃሉ – በአቡነ ጳውሎስ ኅልፈት የተሰማቸውን ሐዘን በጽሑፍ በገለጹበት መዝገብ፡፡
አቦይ ስብሓት ቤተ ክርስቲያን ‹‹የት ነች? ደኅና ነች?›› ብለው መጠየቃቸውን በራሱ በክፋት አናየውም፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን ካለፉት ዘመናት ባልተለየ ኹኔታ ለኻያ አንድ ዓመታት ብሔራዊ ክብሯ ተዋርዶና ተቋማዊ ነጻነቷ ተደፍሮ እንድትዳከም የተደረገችው÷‹‹ኦርቶዶክሱን ማምከን ሙስሊሙን ማስከተት›› /Neutralizing the Church and Mobilizing Muslimsበሚለው የእነ አቦይ የበረሓ ስትራቴጂ መኾኑን ስናስብ ግን ምናልባትም ጸጽቷቸው አልያም ከአቡነ ጳውሎስ የቀረውን የቤት ሥራ ‹ለማስቀጠል› ሊኾን ስለሚችል በጥንቃቄ እንመለከተዋለን፡፡ አሁን በቅርቡ እንኳ‹‹ከአማርኛ ተናጋሪዎችና ከኦርቶዶክስ አማኞች ለማጽዳት ›› ማለታቸው መች የሚረሳ ነው!!

አቦይ ስብሓት በሐዘን መግለጫቸው ‹‹ከአቡነ ጳውሎስ ኅልፈት በኋላ አመቺ ኹኔታ የተፈጠረ ይመስለኛል›› ቢሉም በአቡነ ጳውሎስ ‹ሌጋሲ› (በእርሳቸው አገላለጽ ትተውልን በሄዱት ካህናትና ጳጳሳት) ግና ጥርጣሬ ያላቸው ይመስላሉ፡፡ የካህናቶችዋ መንፈሳዊ ብቃትና አንድነት ጉዳይ ለአቦይ ስብሓት ጥያቄ ነው፤ ከ‹‹ጠባብነትና ትምክህት›› ነጻ መኾናቸውም እንዲሁ፡፡ የትምክህተኝነቱ ባይገባንም የጠባብነቱ ለም አፈር ግን የማን ነገረ ሥራ እንደኾነ ከአቦይ ስብሓት ኅሊና የሚሰወር አይመስለንም፡፡
ከኅትመት ውጪ በኾነችው የፍትሕ ጋዜጣ ‹‹አይረቡም›› ብለው ከሞለጯቸው ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ምን እንደቀራቸው እንጃ እንጂ አቦይ ስለ ጳጳሳቱ አንድነትና ብቃትም የተጨነቁ ይመስላሉ – ‹‹አቡነ ጳውሎስ ትተውልን የሄዱት ቤተ ክርስቲያንና ጳጳሳቱ ደኅና ኹና፣ መሪዎቿም አንድነታቸውን ጠብቀው ብቃታቸው ተጠናክሮ፣ ባጭሩ ጠንካራ ቤተ ክርስቲያን ትተውልን ከኾነ ቅርሳቸው እየተዘከረ ይኖራል፡፡››
አቦይ ስብሓት ስለ ቤተ ክርስቲያኒቱ መጪ ኹኔታ ያሰፈሩልን ሐሳብ እንደ ‹ንግር›/ትንቢት/ ባንቆጥረውም የወቅቱን የሀገር ውስጥና የውጭ ኹኔታችንን በማስተዋል /በአዲስ አበባ ከሀገረ ስብከት መዋቅር ተለይቶ በቦርድ ለመመራት የሚያስቡ አጥቢያዎች አሉ/ እንዲሁም ከጉዳዩ ጋራ በተያያዘ አቦይ የነበራቸውን የቀደመ ቅርበት በማስታወስ እየነዘረ፣ እየጠዘጠዘ እንደማያስተኛ ሕመም ኾኖብናል፡፡ አቦይ እንዲህ ይላሉ÷
ሰው ያልፋል፤ ተፈጥሮ ነው፡፡ አሁን መጠንቀቅ ያለብን ትበታተናለች፡፡ ብዙ
 የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያናት በኢትዮጵያ ሊፈጠሩ ይችላሉና በቅንነት
 ገምግመን እንዴት እንሂድ? እንቀይስ? ጊዜው አሁን ነው፡፡ አመቺ ኹኔታ
  የተፈጠረ ይመስለኛል፡፡
ስብሓት ነጋ ስለ አቡነ ጳውሎስ ኅልፈት በጽሑፍ ያሰፈሩት የሐዘን መግለጫ
ስብሓት ነጋ ስለ አቡነ ጳውሎስ ኅልፈት በጽሑፍ ያሰፈሩት የሐዘን መግለጫ
አቡነ ጳውሎስ ‹‹ሰውና ወንድም በመኾናቸው›› ዕረፍታቸው በጣም እንደሚያሳዝናቸው በሐዘን መግለጫቸው መግቢያ ላይ የገለጹት አቦይ ስብሓት የሐዘን መግለጫቸውን ሲያጠናቅቁ ‹‹ነፍሳቸውን ይማርልን›› በማለት ተሰናብተዋል፡፡ ለሊቃነ ጳጳሳቱ ግን መልእክት አላቸው÷ ‹‹ዋና ነገር ምሕረት ለቤተ ክርስቲያኒቱ፡፡ በሂወት ያላችኹ ጳጳሳት ምሕረትን አውርዱላት፡፡››
አቶ ስብሓት ነጋ ስለ አቡነ ጳውሎስ ኅልፈት በጽሑፍ ያሰፈሩት የሐዘን መግለጫ
አቡነ ጳውሎስ ሰውና ወንድም በመኾናቸው ዕረፍታቸው በጣም ያሳዝነናል፤ ያሳዝነኛል፡፡ ትተውልን የሄዱት ቤተ ክርስቲያንና ጳጳሳቱ ደኅና ኹና፣ መሪዎቿም አንድነታቸውን ጠብቀው፣ ብቃታቸው ተጠናክሮ፣ ባጭሩ ጠንካራ ቤተ ክርስቲያን ትተውልን ከኾነ ደሞ ቅርሳቸው እየተዘከረ ይኖራል፡፡ ቤተ ክርስቲያኒቱ ሃገራዊ ግዴታዋን ስትወጣ የነበረች፣ ለወደፊቱ ታላቅ ሚና ሊኖራት የሚችል ስለኾነች አሁን የት አለች ብለን እናስብ !! ደኅና ናት ወይ? የካህናቶችዋ መንፈሳዊ ብቃትና አንድነትስ? ከጣባብነትና ከትምክህት ነጻ ናቸው? ሰው ያልፋል፤ ተፈጠሮ ነው፡፡ አሁን መጠንቀቅ ያለብን ትበታተናለች፡፡ ብዙ የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያናት በኢትዮጵያ ሊፈጠሩ ይችላሉና በቅንነት ገምግመን እንዴት እንሂድ? እንቀይስ? ጊዜው አሁን ነው፡፡ አመቺ ኹኔታ የተፈጠረ ይመስለኛል፡፡ አቡነ ጳውሎስ ነፍሳቸውን ይማርልን፡፡ ዋና ነገር ምሕረት ለቤተ ክርስቲያኒቱ፡፡ በሂወት ያላችኹ ጳጳሳት ምሕረት አውርዱላት፡፡
ምንጭ፡- ከብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪክ አቡነ ጳውሎስ የ፹ ቀን መታሰቢያ ልዩ እትም መጽሔት
Ab Pawlos 80 Ken
ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪክ አቡነ ጳውሎስ የ፹ ቀን መታሰቢያ ልዩ እትም መጽሔት
Previous Post
Next Post

0 comments: