ኪዳኔ ዓለማየሁ
መግቢያ፤
የኢትዮጵያ የምድር ባቡር ኩባንያ ባለሥልጣን በገለጹት መሠረት፤ ታሪካዊው፤ የሰማእቱ አቡነ ጳውሎስ ኃውልት፤ ለባቡር መንገድ ግንባታ፤ አሁን ካለበት ለጊዜው ተነስቶ፤ ሥራው ከተጠናቀቀ በኋላ፤ ወደ ስፍራው እንደሚመለስ አስታውቀዋል። ቢሆንም፤ ያልተመለሱ ብዙ ጥያቄዎች አሉ። ይህ ከፍተኛ ጉዳይ በተለይ የሚመለከታቸው ድርጅቶች ለምን ዝም አሉ?! የኢትዮጵያ የሕዝብ ምክር ቤት፤ የሚመለከታቸው የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች፤ የኢትዮጵያ ኦርቶቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፤ የኢትዮጵያ አርበኞች ማሕበር፤ የኢትዮጵያ ቅርሶች ጉዳይ ድርጅት፤ የአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት፤ ወዘተ፤ በጉዳዩ ተመካክረው ወስነዋል? ከሆነስ፤ ድምጻቸው ለምን አልተሰማም፤ ለሕዝብስ በቅድሚያ ለምን በግልጽ አልተነገረም? የሐገር ቅርስ ስለ ሆነው፤ የአቡነ ጴጥሮስ ኃውልት ጉዳይ፤ መናገር ያለበት፤ የባቡር ኩባንያ ነው? ለመሆኑ፤ ኃውልቱ ከቦታው መነሳት ካለበት፤ መቼ ተነስቶ፤ መቼ ይመለሳል?
አቡነ ጴጥሮስ ማን ነበሩ?
አቡነ ጴጥሮስ፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጳጳስ የነበሩ፤ በኢትዮጵያዊነታቸው፤ የኢጣልያን ፋሺሽቶችን በግልጽ በመቃወምና በማውገዛቸው ምክንያት፤ ለሐገራቸው ክብርና ነጻነት የተሰዉ፤ የኢትዮጵያ ጀግና ሰማእት ናቸው። ለዚህም ነው፤ በፋሺሽቶች ጥይት በተረሸኑበት አካባቢ፤ ተገቢ የሆነ ኃውልት የቆመላቸው። ስለዚህ፤ የአቡነ ጴጥሮስ ኃውልት፤ ለማንኛውም ኢትዮጵያዊ፤ እጅግ የተከበረ፤ ታሪካዊ ቅርስ ስለ ሆነ፤ እንደ ተራ እቃ፤ የሚነሳና የሚንገዋለል አይደለም።
ስለ አቡነ ጴጥሮስ፤ በጥቂቱ ለመተረክ፤ በ1885 ዓ/ም ፍቼ ከተማ ተወልደው፤ የዓለም ስማቸውም፤ ኃይለ ማርያም ነበረ። በ1909 ዓ/ም መንኩሰው፤ “በ1910 ዓ/ም በወላሞ ወረዳ የደብረ መንክራት ገዳም መምህር ተብለው ተሾሙ። በ1916 ዓ/ም በዝዋይ ደሴት የገዳሙ መምህር ሆኑ። በ1921 ዓ/ም በእስክንድርያ ቅዱስ ማርቆስ ከአራት ጳጳሳት ጋር ጳጳስ ሲሆኑ ስማቸውም ጴጥሮስ ተባለ።” (ጳዎሎስ ኞኞ፤ “የኢትዮጵያና የኢጣልያ ጦርነት”፤ ገጽ 156)። በኢጣልያ ወረራ ዘመን፤ አቡነ ጴጥሮስ ከኢትዮጵያ አርበኞች ጋር ዘምተው ነበር። አቡነ ጴጥሮስ በፋሺሽቶቹ ከተማረኩ በኋላ፤ በተፈረደባቸው መሠረት፤ ሐምሌ 22 ቀን 1928 ዓ/ም፤ አዲስ አበባ ከተማ፤ አሁን ኃውልታቸው በሚገኝበት ሥፍራ አጠገብ፤ በጥይት ተደብድበው ተገደሉ።
ቸሩ፤ የኢትዮጵያ አምላክ፤ የብፁዕ አባታችንን ነፍስ፤ ከጻድቃን ከሰማእታት ጋር፤ በገነት እንደሚያኖርልን እናምናለን።
ፋሺሽቶች በኢትዮጵያ ላይ የፈጸሙት የጦር ወንጀል፤
እ.ኤ.አ. ከ1935-41፤ የኢጣልያ ፋሺሽቶች፤ በቫቲካን መንግሥት ያልተቆጠበ ድጋፍ፤ ኢትዮጵያን በወረሩበት ዘመን፤ ከፈጸሟቸው እጅግ ብዙ የጦር ወንጀሎችና ግፎች፤ ከብዙ በጥቂቱ፤
1ኛ/ በብዙ አውሮፕላኖች በተነሰነሰ የጋዝ መርዝ፤ በቦምብ፤ በጥይት፤ በመድፍ፤ ወዘተ፤ አንድ ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ተጨፍጭፈው ነበር። ከነዚሁ ውስጥ፤ አቡነ ጴጥሮስ፤ አቡነ ሚካኤል፤ ከ400 በላይ የደብረ ሊባኖስ ገዳም መነኮሳት፤ በተለይም፤ በሶስት ቀኖች ብቻ፤ አዲስ አበባ ከተማ፤ 30 000 ኢትዮጵያውያን ተጨፍጭፈዋል።
2ኛ/ 2000 ቤተ ክርስቲያኖችና 525 000 ቤቶች እንዲሁም 14 ሚሊዮን እንስሶች ተደምስሰዋል።
3ኛ/ አሁንም፤ በኢጣልያን ፋሺሽቶችና በቫቲካን ይዞታዎች የሚገኙ፤ እጅግ ብዙ የኢትዮጵያ ንብረቶች ተዘርፈዋል። ከነዚሁ ውስጥ፤ ከ500 በላይ የሆኑ ታሪካዊ ሰነዶች፤ በቫቲካን ቤተ መዛግብት፤ እንዲሁም “ፀሀይ” ትሰኝ የነበረች ትንሽ አውሮፕላን፤ በኢጣልያ አየር ኃይል ቤተ መዘክር እንደሚገኙ ተገልጿል።
ከኢጣልያና ከቫቲካን መንግሥቶች ስለሚፈለገው ካሣ፤
ኢጣልያና ቫቲካን፤ እጅና ጓንት ሆነው፤ ኢትዮጵያ ላይ ለተፈጸመው፤ እጅግ ከባድና አሰቃቂ እልቂትና ውድመት፤ ተገቢው ካሣ እስካሁን አልተከፈለም። “በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” እንደሚባለው፤ ከዚህ በፊት፤ በኢትዮጵያ ላይ የተፈጸመው ግፍ ሁሉ አልበቃ ብሎ፤ የኢጣልያ መንግሥት፤ በቅርቡ፤ “የኢትዮጵያ ጨፍጫፊ” በመባል ለሚታወቀው፤ ለሮዶልፎ ግራዚያኒ፤ ከሮም ወደ ደቡብ በምትገኝ፤ አፊሌ በምትሰኝ ከተማ፤ አንድ መካነ-መቃብርና መናፈሻ ሥፍራ አቋቁሞለታል። የቫቲካን መንግሥትም፤ ሙሶሊኒንና የፋሺሽት መንግሥቱን ይደግፉ ለነበሩት፤ ለፖፕ ፓየስ 12ኛ፤ የቅድስና ማእረግ ለመስጠት በሒደት ላይ መሆኗ ተገልጿል። ይህንን በተመለከተ፤ “Why is the Vatican Adding Insult to Injury on Ethiopia” በተሰኘ አርእስት በዚህ ጸሐፊ የቀረበውን ከGoogle ማግኘት ይቻላል።
እነዚህን ኢሰብአዊና ኢፍትሐዊ ድርጊቶች በተመለከተ፤ Global Alliance for Justice – The Ethiopian Cause (www.globalallianceforethiopia.org) የተሰኘው ድርጅት ከዚህ በታች የተዘረዘሩት እንዲከናወኑ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል፤
1ኛ/ የቫቲካን መንግሥት፤ በሐገራችን ላይ ከፍተኛ የጦር ወንጀል ለፈጸመው፤ የኢጣልያ መንግሥት፤ ስላከናወነችው ድጋፍ፤ ጦሩንም በመባረኳ፤ የኢትዮጵያን ሕዝብ ይቅርታእንድትጠይቅ፤ (ይህንን በተመለከተ፤ በwww.globalallianceforethiopia.org ላይ አንድ ዓለም-አቀፋዊ የሆነ አቤቱታ እየተፈረመ ነው።)
የቫቲካን ካሕን የፋሺሽቱን ጦር ሲባርኩ
2ኛ/ የኢጣልያን መንግሥት፤ በኢትዮጵያ ላይ ለፈጸመችው ከፍተኛ የጦር ወንጀል፤ ተገቢውን ካሣ እንድትከፍል፤ (ይህንን በተመለከተ፤ በቅርቡ፤ የኢጣልያን መንግሥት፤ ለሊቢያ፤ $5 ቢሊዮን ለመክፈል መስማማቱ ተገልጿል። ይህንንም የሚያደርግበት ምክንያት፤ በሊቢያ ላይ ለፈጸመው ወንጀል ብቻ ሳይሆን፤ 30 000 ሊቢያውያን ወታደሮችን ኢትዮጵያ ላይ በማዝመቱ ነው። እጅግ የሚያስደንቀው፤ አንድ ሚሊዮን ሕዝብ ለተጨፈጨፈባትና ሌላም ከፍተኛ ውድመት ለደረሰባት ኢትዮጵያ፤ “ካሣ” ተብሎ የተከፈለው፤ ቆቃ ግድብ የተሠራበት፤ 6 ሚሊዮን ስተርሊንግ ፓውንድ ብቻ መሆኑ ነው። ይህ ክፍያ በምንም መስፈርት በቂ ስላልሆነ፤ በኢትዮጵያ ላይ ለተፈጸመው ግፍ ተገቢ ፍትሕ እስኪገኝ ድረስ፤ ትግሉ መቀጠል አለበት።)
3ኛ/ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፤ ኢጣልያኖች በኢትዮጵያ ላይ የፈጸሙትን የጦር ወንጀል በሰነዱ እንዲያውለው፤
4ኛ/ ከኢትዮጵያ የተዘረፉት ንብረቶች በኢጣልያና በቫቲካን ለኢትዮጵያ ሕዝብ እንዲመለሱና
5ኛ/ በቅርቡ፤ ለጦር ወንጀለኛው፤ ለሮዶልፎ ግራዚያኒ፤ የቫቲካን ተወካይ በተገኙበት፤ በአፊሌ የተመረቀው መካነ-መቃብርና መናፈሻ፤ እንዲፈርስ ተጠይቋል። ስለዚህ ጉዳይ፤ ብዙ ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች፤ ከፍተኛ የድጋፍ እንቅስቃሴ አከናውነዋል። መካነ-መቃብሩ እንዲወገድ፤ በአፊሌ (ኢጣልያ)፤ በለንደን፤ በዋሺንግተን ዲ.ሲ ሰላማዊ ሰልፎች ያከናወኑት ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች እንዲሁም የኢትዮጵያ አርበኞች ማሕበር፤ የኢትዮጵያ የጥናት ማእከል፤ በዳላስ ከተማ የኢትዮጵያውያን መረዳጃ ማሕበር፤ ወዘተ፤ ተቁዋሟቸውን በመግለጻቸው ልዩ ምሥጋና ይገባቸዋል። ለኢጣልያ ፕሬዚዳንትና ጠቅላይ ሚኒስትር የተጻፈውን የተቃውሞ ደብዳቤ፤ ከላይ በተጠቀሰው ድረ-ገጽ ማየት ይቻላል።
ለግራዚያኒ መታሰቢያ ሲመረቅ፤ የአቡነ ጴጥሮስ ኃውልት መነሳት ጉድ!
ያጋጣሚ ነገር ቢሆንም፤ ባንድ ሰሞን፤ ለጦር ወንጀለኛው፤ ለግራዚያኒ መታሰቢያ ተመርቆ ሳለ፤ እርሱ ላስገደላቸው ለጀግናው ሰማእት፤ ለአቡነ ጴጥሮስ፤ ቆሞ የነበረው ኃውልት፤ ለጊዜውም ቢሆን፤ እንዲነሳ መደረጉ ማንንም ያስደንቃል።
ስለ አቡነ ጴጥሮስ ኃውልት መነሳት መመለስ የሚያስፈልጋቸው ጥያቄዎች፤
1ኛ/ የባቡሩን ሐዲድ ለመሥራት፤ የአቡነ ጴጥሮስን ኃውልት ከማንሳት ሌላ፤ ተቀባይነት ያለው፤ አማራጭ አለ?
2ኛ/ የአቡነ ጴጥሮስ ኃውልት መነሳት፤ የሕዝብን ስሜት የሚነካ፤ ከፍ ያለ ጥንቃቄ የሚገባው ጉዳይ በመሆኑ፤ ለምን፤ በቅድሚያ ሕዝባዊ ምክክር አልተከናወነም?
3ኛ/ ጉዳዩ፤ በተለይ የሚመለከታቸው ድርጅቶች፤ ለምሳሌ፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፤ የኢትዮጵያ አርበኞች ማሕበር፤ የአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት፤ የኢትዮጵያ ቅርሶች ጥበቃ ድርጅት፤ የማስታወቂያ ሚኒስቴር፤ ወዘተ፤ ለምን ዝምታን መረጡ?
4ኛ/ ስለ ሐገር ታሪክ፤ ክብርና ፍትሕ እንጨነቃለን የሚሉት የፖለቲካ ድርጅቶችስ ምነው ድምጻቸውን አጠፉ?
መፍትሔ፤
ከላይ እንደ ተጠቀሰው፤ የአቡነ ጴጥሮስ ኃውልት፤ በኢትዮጵያ ሕዝብ ልብና አስተሳሰብ፤ ልዩ ግምት ያለው የሐገር ቅርስ ነው። እንደ ተራ እቃ ሊቆጠር አይገባውም። ስለዚህ፤ የሚመለከታቸው ድርጅቶች፤ በተገቢ ባለሙያተኞች እየታገዙ፤ ግልጽ ውይይት አከናውነው፤ የሕዝብ አመኔታ በሚያስገኝ ሒደት፤ በትክክለኛ ውሳኔ፤ ተገቢ እርምጃ እንዲወሰድ ያስፈልጋል። የአቡነ ጴጥሮስ ኃውልት፤ ለኢትዮጵያ ሕዝብ (ለክርስቲያኑም፤ ለእስላሙም፤ ለሁሉም)፤ የነጻነት፤ የጀግንነት፤ የአርበኛነትና የአለኝታነት ነጸብራቅ መሆኑና ከትውልድ እስከ ትውልድ የሚታሰብና የሚዘከር መሆኑ መታወቅ አለበት።
08,Decemeber 2012
ECADF NEWS
0 comments: